በአውሮፓ ኅብረት የስኳር በሽታ ጥናት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የቀረቡ አዳዲስ የጥናት ውጤቶች እንደሚያመለክከቱት ከሆነ፥ በአዋቂዎች ውስጥ የሚታይ ዓይነት 2 የስኳር በሽታ መነሻው የሶዲየም መጠን መብዛት መሆኑን ያመለክታሉ።
ይህም የሆነው ሶዲየም በኢንሱሊን የመቋቋም አቅም ላይ ተፅእኖ ስለሚያሳድር ነው ተብሏል።
ተመራማሪዎቹ እንዳሉት በየቀኑ መውሰድ ከሚገባን ሶዲየም ላይ ተጨማሪ 2 ነጥብ 5 ግራም በወሰድን ቁጥር ዓይነት 2 ለተባለው የስኳር በሽታ የመጋለጥ እድላችንን በ43 በመቶ ይጨምራል።
በማደግ ላይ ባሉ አገራት ደግሞ አንዳንድ ግራም ተጨማሪ ሶዶየም በተወሰደ ቁጥር ለበሽታው የመጋለጥ እድል 73 በመቶ ነው።
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል እንደገለፀው የስኳር በሽታ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ29 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎችን ያጠቃል።
ከዚህ ቁጥር 95 በመቶ የሚሆኑት ዓይነት 2 በተባለው የስኳር በሽታ የተያዙ ናቸው።
የዚህ ዓይነቱ የስኳር ህመም በአብዛኛው በመካከለኛ እና በዕድሜ ባለፀጋዎች ውስጥ እንደሚታይም ተነግሯል።
ተመራማሪዎቹ በጨው ውስጥ የሚገባው የሶዲየም መጠን የስኳር በሽታ ስለሚያባብስ ከዚህ መጠንቀቅ እንደሚገባ መክረዋል።