የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረው አሰግድ ተስፋዬ በድንገት አረፈ

(ቅዳሜ ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. June 3, 2017)፦ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የእግር ኳስ ተጫዋች የነበረው አሰግድ ተስፋዬ፤ በዛሬው ዕለት ከልምምድ መልስ በመታጠቢያ ቤት ውስጥ ወድቆ

በአርባ ሰባት ዓመቱ በድንገት ሕይወቱ አለፈ። ሥርዓተ ቀብሩ ሰኞ ግንቦት ፳፰ ቀን ከሰዓት በኋላ በስምንት ሰዓት በቅድስት ሳህሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን ይፈጸማል።

አሰግድ ተስፋዬ በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ ነበር የተወለደው። እድገቱም በዚያው በድሬዳዋ ከተማ ልዩ ስሙ ደቻቶ በሚባለው አካባቢ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ወጣት ቡድን፣ ለድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ቡድን፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን፣ ለኢትዮጵያ መድን ቡድን እና ለኢትዮጵያ ቡና ቡድን የፊት መስመር ተጫዋች ነበር።

ታዳጊ ወጣቶችን በእግር ኳስ በማሠልጠን አገሪቱ ስመ-ጥር ተጫዋቾች እንድታፈራ ሳይታክት በመሥራት ላይ የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡም ሲያሠለጥናቸው የነበሩ ታዳጊዎችን ወደ ሰሜን አሜሪካ በመውሰድ የልምድ ልውውጥ አድርጎ እንደነበር የታሪክ መዝገቡ ይመሰክራል። አሰግድ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር።

የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለአሰግድ ተስፋዬ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ አፍቃሪዎች እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን በዚህ አጋጣሚ ይመኛል። በርካቶች የስፖርቱ ቤተሰቦች በአሰግድ ተስፋዬ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ኀዘናቸውን እየገለጹ የሚገኙ ሲሆን፣ የስፖርት ጋዜጠኞቹ ታደለ አሰፋ እና ኢብራሂም ሻፊ አሕመድ በፌስ ቡክ ገጾቻቸው ስለአሰግድ የሚከተለውን አስፍረዋል።

በየትኛው ስምህ ልጥራህ ብዙዎች ብዙ ስም አውጥተውልካል፣ ከደቻቱ እስከ ኮካ ሜዳ በአዲስ አበባ ከቅ/ጊዮርጊስ መድን እና ቡና፣ ከወጣት ቡድን እስከ ብሔራዊ ቡድን ሁሉም በችሎታህ እና በፀባይህ ስምህን አብዝተውታል።
ጅሬስ፣ ሮማሪዮ፣ አሰግድ ፔሌ፣ እስከ መዝገብ ስምህ አሰግድ ተስፋዬ፤ ታዲያ እኔ በየቱ ልጥራህ?
በቃ ሁሌም እንደምለው አሴ ልበል፣ በእግር ኳስ ችሎታህ ማንም አይጠራጠርህም፤ አንተ እና ግብ ከተገናኛችሁ ኳሷ ከመረብ ለማረፍዋ ሁሉም እርግጠኛ ስለሆነ መጨፈር ይጀምራል፤ አሴ ጎል ... አሴ ልስልሱ አንጀት አርሱ ... ብሎም ባንድ ላይ ያዜማል፤ በብቃትህ ሲረካ እናት አባትህ ያወጡልህን ስም ትቶ ጅሬስ፣ ሮማሪዮ፣ አሰግድ ፔሌ ሲል ይጠራኻል።
ከሜዳ ስትወጣ ሁሌም ከራስህ በላይ ለሰው እንደተጨነቅህ፣ ተጫዋች ታመመ፣ ኑሮው ችግር ላይ ነው፣ በቃ በዛም በዚህም ማስተባበር፣ ፈገግታና ቀልድ እንጂ ቂም እና ቁጣህን ሳላይ ተለየኸኝ።
አሴ አንተ ለእኔ እግር ኳስ ተጫዋች ብቻ ሳትሆን፤ የሕይወት ተምሳሌቴም ነበርክ።
አምላክ ነፍስህን በገነት ያኑር!ጋዜጠኛ ታደለ አሰፋ
እግር ኳስ ተጫዋችን ለመለየት አንዲት የኳስ ቁጥጥር (Control) በቂ ነው ብዬ ስከራከር በህሊናዬ ከሚመላለሱ ተጨዋቾች መካከል አንዱ አንተ ነበርክ። ሰውነትህ ትንሽ ቢሆንም ኳስ እግርህ ስትገባ ትገዝፍ ነበር። ሩጫው ብዙም አይደለም ሲሉህ፤ አጭር ርቀት ላይ በመብረቅ ፍጥነት ጥለኻቸው ሄደህ ያስደነገጥካቸው ብዙ ናቸው። በጠባብ ቦታ ኳሱን ደብቀህ ያለፍካቸውን ተከላካዮች ቤት ይቁጠራቸው።
ጎል ፊት እንዳንተ የተረጋጋ እና የሚዘንጥ እስካሁንም በአገሬ ምድር አላየሁም። ተከላካዮችን ላያቸው ላይ ሮጠህ፣ ሽብር ላይ ጥለህ እና ኳሱን ፊት ለፊታቸው ነድተህ ካለፍክ በኋላ፤ ጎሉን ለማወቅ ቅንጣት ስትቸገር አላስተዋልኩም። በቀኝም ሆነ ግራ እግርህ ጎሎችን … ውብ ጎሎችን አግብተሃል። ኳስን ከመቀበልህ በፊት ተከላካዮች እና በረኞች የት እንዳሉ ቅድሚያ እያየህ በአዕምሮ ተጫውተሃል። አደጋ ክልል ኳስን ይዘህ ገባህ ማለት ጎል ተቆጠረ ማለት ነው እስኪባል ድረስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተዓምር አሳይተሃል።
እግርኳስ ግርማ ሞገስህን እንደሚጨምረው ሁሉ፤ አንተም የእግር ኳሱ ውበት ሆነህ ብዙ ዓመታት ዘልቀሃል። ከእግር ኳሱ መለየት ስላልቻልክ መጫወት ካቆምክ በኋላ ሕፃናትን በማሠልጠን የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለመታደግ ብዙ ሞክርሃል። ሜዳ ላይ ግርማ ሞገስ ሰጥቶህ፣ ውበትን የምትመልስለት እግር ኳስ ግን ዛሬ ሕይወትህን ነጥቆሃል። ለጤናህ ተጫውተህ ለመታጠብ ስትገባ በድንገት ወድቀህ ሕይወትህን አሳጥቶሃል። …
አሴ! አንተ ትሁት፣ ተባባሪ፣ ቅን፣ ታማኝ፣ ሠራተኛ፣ ለተቸገረ ደራሽ እና መልካም ሰው ነበርክ። ከሁሉም … ከሁሉም … በኳስ ገዝፈህ፣ ለኳሷ ውበትን የምትመልስ ድንቅ ተጫዋች ነበርክ። … አምላክ ይዘንልህ ጓደኛዬ! … ከመልካም ወዳጅ ስንብት እንዴት ከባድ ነው?!ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ አሕመድ

Share this post

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to StumbleuponSubmit to TechnoratiSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Rate this item
(0 votes)

180291 comments

Leave a comment

Make sure you enter all the required information, indicated by an asterisk (*). HTML code is not allowed.

Information for All

Go to top